በመንፈስ መጸለይ
በጭንቀትና በሀዘን ውስጥ ወይም ግራ በሚገባ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንዴት እንደምንጸልይ አናውቅም፡፡አንዳንዴም የምናወጣቸው ቃላቶች እና አእምሮአችን ልንጸልይ የምንፈልገውን መግለጽ ሊያቅታቸው ይችላል፡፡ቃላት ጸሎታችንን መግለጽ ሲያቅተው በመንፈስ ቅዱስ ላይ በመደገፍ እርሱ በውስጣችን እንዲቃትት ብንፈቅድለት ከፍ ያለ ጸሎት መጸለይ እንችላለን፡፡ሮሜ ፡26-27
ብዙ የስነ-መለኮት አዋቂዎች ሀና በመንፈስ ትጸልይ እንደነበረ ይስማማሉ፡፡(1ሳሙ 1፡12-16)ከንፈሯ ይንቀሳቀስ ነበር ነገር ግን ድምጽዋ አይሰማም ነበር፡፡ስለዚህ ታላቁ የእግዚአብሄር ሰው ኤሊ ተሳስቶ ጠጥታ የሰከረች መሰለው፡፡ሀና ከበድ ባለ ጭንቀት ውስጥ ስለ ነበረች በመንፈስ ትቃትት ነበር፡፡ሃና በአራቱም ማእዘን እየደረሰባት ካለው ፈተና የተነሳ ምሬት ውስጥ ነበረች፡፡በሴትነቷ እና በሚስትነት ማንነቷ ላይ የተነጣጠረ አደጋ ስለነበረ ነው መከራዋን ከበድ ያደረገው፡፡ስለዚህም እግዚአብሄርን በጽኑ ፈለገችው፡፡በመንፈስ ብርቱ ጸሎትን ጸለየች፡፡በዘመኑ ብርቱ የነበረ ሳሙኤልን ወለደች፡፡
እኛም አዳጋች ነገር ሲገጥመን ወደ ጸጋው ዙፋን መጥተን በመንፈስ ብንጸልይና ረዘም ላሉ ሰአታት ብንቃትት ጸሎቱ በቀጥታ ከእግዚአብሄር ጋር ስለሚያገናኘን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ያለ ጸሎትን እንጸልያለን፡፡ችግራችንም በእግዚአብሄር ጊዜ ይንከባለላል፡፡
እግዚአብሄር ሆይ እባክህ የጸሎትን ሚስጥር ግለጥልን!