Monday, August 12, 2013

የጸሎት ጥልቀት(ተግባራዊ እርምጃ)






የጸሎት ጥልቀት(ተግባራዊ እርምጃ)

ረዘም ያለ ጸሎትን ስናስብ ምንም ብዙ ጊዜ በስጋ ብንጀምርም በመንፈስ እንደምንጨርስ በመተማመንና በጸሎታችንም ድንቅ ነገርን እንደምናይ ተስፋ በማድረግ በጌታ ፊት እንውደቅ፡፡ቶሎ እንድናቋርጥ እና ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንድንሄድ ወደ ነፍሳችን ግብዣዎች ይመጣሉና እነዚህን መንፈስን የማያረጋጉ መልእክቶች ወደ ጎን በማድረግና በመጨከን በጸሎት እንገስግስ፡፡
ስለ ጸሎት ጥሩ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ጸሎት ከሶስት በላይ እርከኖች (dimensions)እንዳሉት ይናገራሉ፡፡እነርሱም፡-
1.የውጨኛው አደባባይ(the outer court)
2.ቅድስት/መሀከለኛው አደባባይ(holy/the middle court)
3.ውስጠኛው አደባባይ/ቅድስተ ቅዱሳን(holy of holies)
ብዙዎቻችን በጸሎት ጊዜያችን የውጨኛውን አደባባይ ተሳልመንና የጌታን ጸጋ ሳንካፈልና በረከቱን ሳናይ ነው የምናቋርጠው ምንም እንኳ ዲሲፕሊን እንደሚያስፈልገን ብናምንም፡፡ለዚህ መፍትሄው ጽኑ የሆነ ውሳኔና መጨከን ነው፡፡ደጋግመን ስናደርገው ትግል መሆኑም ይቀራል፡፡
እነዚህ የጸሎት እርከኖች(dimensions) ሉቃስ 119 ላይ በሚገባን ሁኔታ ተቀምጠዋል፡፡እነርሱም -
1.መጠየቅ (the asking realm)፡የመጀመሪያና ብዙ ትግል የሌለው በአእምሮአችን የምንጸልየው ጸሎት
2.ፊቱን መፈለግ(the seeking realm)፡በመጠኑም ቢሆን ጠንከር ያለና መንፈሱ እስኪሰማን(recognize) ድረስ የምንጸልየው ጸሎት ነው
3.ማንኳኳት(the knocking realm)፡በጣም የጠለቀ እና በመንፈስ የሚጸለይ ጸሎት እና ብዙ ጊዜ ዝምታ የሚበዛው ጸሎት ነው
እንዳውም ይኸው ቃል ወረድ ብሎ ቀጥር 10 ላይ እንደ ተስፋ ቃል ሆኖ ተቀምጧል፡፡እንዲህ ይነበባል፡-‹‹የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤የሚፈልግም ያገኛል፤መዝጊያን ለሚያንኳኳውም ይከፈትለታል፡፡›› የሚገርም የተስፋ ቃል ነው በሕይወቴም ሲሰራ ስላየሁት ያስደንቀኛል፡፡ስለዚህ የእግዚአብሄር መንፈስ እንደሚመራን ሆነን ድምጹን እየሰማን፣ እየታዘዘንና እጃችንን ይዞ እንዲመራን ከፈቀደልንለትና እርግት ብለን በቂ ገዜ በፊቱ ብንሆን ግሩም ጊዜዎችን እናሳልፋለን ህብረታችንም ይጠልቃል፡፡ባጭሩ ልንወስድ የሚገባን ተግባራዊ እርምጃዎች(የራሴን ልምድ ላካፍላችሁ እናንተ ከኔ የተሻሉ መንገዶች ሊኖሯችሁ ይችላል)-
·       ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ጸሎቶችን እንዳንጸልይና የእግዚአብሄርን ሙሉ በረከት እንዳንቀበል የሚያረገን የጠላት ተጽእኖ ሊሆን ይችላል፡፡ስለዚህ በመንፈስ በመለየት በሀይል እየተቃወምንም መጸለይ አለብን፡፡
·       በተጨማሪም የጸሎትና የአምልኮ መዝሙሮችን ከፍተን  መንፈሳችን እንዲነቃቃና እንዲቀጣጠል ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡
·       ሌላው በመሀል መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ከምንጸልይባቸው ሁኔታዎች ጋር የሚሄዱ ቃሎችን በማንበብና  በጸሎት መንፈስ ሆነን በማሰላሰል የበለጠ መንፈሳችንን ለቀጣይ ጸሎት ሊነሳሳ ይችላል፡፡
·       አእምሮአችን እንዳይሰባሰብ የሚያደርጉ በግል የምናውቃቸውን ነገሮች በውሳኔ ከአካባቢያችን ማራቅ (ለምሳሌ ሞባይላችንን ማጥፋት)
ትልቁ ነገር ግን ውሳኔ ነው፡፡እኔ ቢሰማኝም ባይሰማኝም አልነሳም ከጸሎት ብዬ የምወስንባቸው ጊዜዎች አሉ፡፡እንዳውም እንዳልጸልይ በከበደኝ ጊዜ ገፍቼ ብዙ ሰኣት በውሳኔ ስጸልይ ካሰብሁት በላይ አስደናቂ ጊዜን አሳልፌ አውቃለሁ፡፡ተቁነጥንጠን ስንነሳ ያንኑ የምናውቀውን ህይወትና ኑሮ ነው የምንቀጥለው ከጌታ ጋር ብናሳልፍ ግን ህይወታችን እየተለወጠና የጌታ ጸጋ በሕይወታችን እያደገ ይመጣል፡፡አለበለዚያ ልንመኝ ልናስመስል እና ዝም ብሎ በባዶው ልንጓጓ እንችል ይሆናል እንጂ በነካ ነካ ጸሎት የእግዚአብሄርን ክብርና ጉብኝቱን አናይም፡፡ ስለዚህ መልካሚቱ እጁ በመካከላችን እንድትበዛ በጸሎት መጋደል አለብን፡፡
ጸሎት -ጌታ ሆይ ከዳር ዳር ጸሎት እባክህ ክብርህን ወደምናይበት ጥልቀት ውስጥ ክተተን!






No comments:

Post a Comment