የልቅሶው ሸለቆ በረከት
መከራንና ችግርን የሚፈልግ ማንም የለም፡፡ነገር ግን ነባራዊ ሀቅ በመሆኑ መከራ ችግርና ስብራት
ወደ ህይወታችን ይመጣሉ፡፡በዚህ ጊዜ የሚኖረን እይታ ማስተዋልና ምላሽ ቀጣይ የህይወታችንን ሂደት በሀይል ይወስኑታል፡፡
መከራ ችግርንና ስብራት ተገቢ በሆነ ምላሽና በእግዚአብሄር ቃልና መርህ ተንተርሰን ከተጋፈጥናቸው
ብሎም እግዚአብሄር በነገሮቹ ውስጥ አብሮን እንዳለና ሊያወጣን የታመነ አምላክ እንደሆነ ማሰብ ከቻልን ከግማሽ በላይ እነዚያን ገጠመኞች
ሳንጀምር አሸንፈናቸዋል ማለት ይቻላል፡፡
በእንደዚህ አይነት ወቅት በጌታ ፊት የምናሳልፋቸው ጊዜያት እጅግ ወርቅ ናቸው፡፡ይሄ ጊዜ በሃይል
የምንሰራበት እና እምነታችንና የትእግስታችን ደረጃ የሚፈተሹበትና ለማደግም የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡
መዝ 84፡6 ላይ የሚያስደንቀኝና በሀይል የምወደው ቃል አለ፡፡እርሱም እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹በልቅሶ ሸለቆ በወሰነው ስፍራ የህግ መምህር በረከትን ይሰጣልና ከሀይል ወደ ሀይል ይሄዳሉ፡፡››በወሰነው
ስፍራ የሚለው የዚህ ቃል የአረፍተ ነገሩ ቁልፍ ቃል ይመስለኛል፡፡በዚያ ሂደት ውስጥ ጌታ በምህረቱ እስኪገለጥና ነፍሱ የወደደችው
ሀሳብና ስራ እስኪያበቃ በፊቱ መሆን እንደሚያስፈልግና ከጉስቁልናው ጫና የተነሳ ስፍራ መልቀቅ እንደሌለብን ነው የሚያስገነዝበን፡፡ቃሉ
ሰዋዊ መፍትሄዎችንም እንዳናተራምስና እርፍ እንድል ነው የሚያመለክተን፡፡
በሸለቆ ውስጥ በጽናት ፊቱን እየፈለግን ቃሉን እየተመገብን በቂ ጊዜን ስንወስድ የሚመጣ በረከት
እንዳለ ቃሉ በሚገባ ያሳየናል፡፡በረከቱም ከሀይል ወደ ሀይል መሄዳችን ነው፡፡ማለትም መንፈሳችን ይጠነክራል፤እግዚአብሄር በሚዳሰስ
መልኩ እናውቀዋለን፤እምነታችን የሚጠነክርበትና ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ የሚልበት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
ከዚህ ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነ የምወደው ሌላ ቃል አለ፡፡እርሱም ኢሳ40፡31 ላይ ይገኛል፡፡እንዲህ
ይላል፡-‹‹እግዚአብሄርን በመተማመን የሚጠባበቁ ሀይላቸውን ያድሳሉ፡፡››እግዚአብሄርን እንደሚያሳልፈንና እንደሚያሻግረን በመተማመን
በቂ ጊዜ እየወሰድን በጸጋው ዙፋን ፊት ወድቀን ስንቃትትና ጉብኝቱን ስንጠባበቅ በራሱ ጊዜ እና በመለኮታዊ ጥበቡ ተገልጦ ያስደንቀናል፡፡ችግራችንና
መከራችንም ይወገዳል፡፡ትልቁ ነገር ግን መንፈሳዊ ሀይላችን ይጨምራል፡፡ለሌሎችም የሚነበብ ምስክር እንሆናለን፡፡እግዚአብሄር እንደዚህ
እንድናይ ይርዳን!
No comments:
Post a Comment